የኢቴቪ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራቸው ለቀቁ

በርካታ ጋዜጠኞች በለውጡ ደስተኞች ሆነዋል
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) ሦስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በቅርቡ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ አሸብር ጌትነት፣ የትምህርታዊ ፕሮግራሞች ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ተመስገን ገ/ህይወት፣ የመዝናኛ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ፍቅር ይልቃል በወራት ልዩነት ድርጅቱን መልቀቃቸው ታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ከጥር ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከኃላፊነታቸው ተነስተው በኢቴቪ ከተሾሙ በኋላ የድርጅቱን የአሠራር ሥርዓት ለማስተካከል የወሰዱት ጠንካራ እርምጃዎች በኃላፊዎቹ እንዳልተወደደ ምንጮች ተናግረዋል።
በኢቴቪ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሚደረጉ የውጪ አገር ጉዞዎች በጥቂት ግለሰቦች ሞኖፖሊ ብቻ ተይዞ የቆየ ሲሆን፤ አዲሱ ዳይሬክተር ይህን አሰራር በመሰረዝ የሚመለከታቸው ሪፖርተሮች በየተራ ተመድበው እንዲሰሩበት ማድረጋቸው፣ አንዳንድ ኃላፊዎች የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ኢቴቪ ውስጥ እየሰሩ በግል ድርጅታቸው አማካይነት ሥራዎችን ለመወዳደር ማመልከታቸውና ይህም ተቀባይነት ማጣቱ፣ እንዲሁም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ክፍት የነበሩ አሰራሮች እየተዘጉ መምጣታቸው ኃላፊዎቹን ሳያበሳጭ እንዳልቀረ ምንጮቹ ጠቁመዋል።
አንድ የድርጅቱ ባልደረባ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገረው፤ አዲሱ ማኔጅመንት ሥር ነቀል ለውጥ እያደረገ መምጣቱ በአብዛኛዎቹ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ዘንድ ድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል። አንዳንድ ኃላፊዎች ያለ ችሎታቸው ጭምር ተመድበው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደነበርና ይህም በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታ ሲቀርብበት ነበር ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ይህ ሁኔታ አሁን እንዲስተካከል መደረጉ አስደስቶናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የሚካሄደው ለውጥ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣይ ሕዝባዊ ሚዲያ ለመፍጠር የሚያስችል ይሆናል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
    ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ደረጃ እንዲያድግ የሚደነግገውን አዋጅ ተቀብሎ ማጽደቁ ይታወሳል።
Advertisements

ሸራተን ሆቴል ብዛት ያላቸውን ሰራተኞቹን አባረረ

July 31, 2014

በሼህ አላሙዲን ሜድሮክ ኩባንያ ስር የሚገኘው ሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዳደር ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር ለአመታት የዘለቀ ግጭት ውስጥ መክረሙን የሚያስታውሱት ምንጮች በዛሬው ዕለት አስተዳደሩ የማህበሩን አመራሮች ጨምሮ በስራ ገበታቸው ተገኝተው የነበሩ ብዛት ያላቸውን ሰራተኞች ‹‹ሆቴሉ ከእናንተ ጋር የነበረውን የስራ ኮንትራት አቋርጧል››የሚል ወረቀት በመስጠት ከ15 ዓመታት ያላነሰ ድርጅቱን ያገለገሉ ሰራተኞቹን ማባረሩ ታውቋል፡፡
የስራ ዩኒፎርም ለብሰው ወደ ስራቸው ለመግባት ይዘጋጁ የነበሩት ሰራተኞች ወደ ቢሮ ተጠርተው ወረቀቱን መቀበላቸውን እንዲፈርሙ እየተደረጉና በሆቴሉ የጥበቃ ሰራተኞች ታጅበው ግቢውን እንዲለቁ መደረጋቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
መረጃውን ተከትሎ ወደ ሆቴሉ አስተዳደር ስልክ ብደውልም ሃላፊ የተሰኙት ሰው ስማቸውንና በሆቴሉ ውስጥ ያላቸውን የስራ ድርሻ ጨምሮ ድንገተኛው የሰራተኛ ስንብት ስለመፈጸሙ ወይም ስላለመፈጸሙ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑልኝ ቀርተዋል፡፡

አልሲሲና እስራኤል ምን እና ምን ናቸዉ?

የእሥራኤል ጦር የጋዛ ሠላማዊ ሕዝብን መግደል፤ ማቁሠል፤ ማሰቃየቱን የሚቃወመዉ ሕዝብ ባለፈዉ ሳምንት ከቺካጎ-እስከ ለንደን፤ ከፓሪስ እስከ ኢስታንቡል፤ ከበርሊን እስከ ቴሕራን የሚገኙ አደባባዮችን በሠልፍ አጥልቅልቋቸዉ ሰነበተ።የእሥራኤል ደጋፊዎችም ተሠልፈዋል።ግን ቁጥሩ ከተቃዋሚዎቹን አንፃር ኢምንት የሚባል አይነት ነበር።ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፤ ሊባኖስ፤ ዱባይ ሌላዉ ቀርቶ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ሮኬት በሚወርድባት ቴል አቪቭም የእሥራኤልን መንግሥት በመቃወም-አደባባይ የወጡ ነበሩ።

እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የሠሞኑን አይነት ርምጃ በወሰደች ቁጥር ለፍልስጤሞች መቆርቆሩን ከማንም ቀድሞ የሚገልጠዉ የግብፅ ሕዝብ ነበር።የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን መንግሥት ባለፉት ሰወስት ሳምንታት በጋዛ ሕዝብ ላይ የወሰደና የሚወስደዉን ርምጃ የአዉሮጳ፤ አሜሪካ፤ የቱርክ-ፋርስ ሕዝብ አይደለም ቁጥራቸዉ አናሳ ቢሆንም የየሩሳሌሙ ነዋሪ ያይር ሐኮሕንን የመሳሰሉ እስራኤላዉያን ሳይቀሩ ተቃዉመዉታል።
«እንደሚመስለኝ የፍልስጤሞችን ጥያቄ በመዘንጋታችንና በመታበያችን አሁን ዋጋ እየከፈልን ነዉ። በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን መፈናፈኛ አሳጥተን መቆየት እንደማንችልና እንደማያዛልቀን ልንገነዘበዉ ይገባል።»
በሕዝብ ብዛትም፤ በጦር ሐይል ትልቅነትም ከአረቦች ቀዳሚዉን ሥፍራ ከምትይዘዉ፤ ለጋዛ ሕዝብ ከጋዛዎች ቀጥሎ ከማንም በላይ ታሪካዊ፤ ፖለቲካዊ፤ መልከዓ ምድራዊ ሐላፊነት ያለባት የግብፅ ገዢዎች ግን የእስራኤል እርምጃ ሊቃወሙ ቀርቶ ተራዉ ሕዝብ በአደባባይ እንዲቃወም እንኳን አልፈቀዱለትም።
ምክንያት እሥራኤል ላይ ሮኬት የሚያወነጭፈዉ ሐማስ የግብፁ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር ቅርንጫፍ ወይም ጥብቅ ወዳጅ ነዉ።በግብፅ ሕዝብ የተመረጡትን የሙስሊም ወንድማማቾቹን ፖለቲከኛ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን ያስወገዱት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ የሙስሊም ወድማማች ጠላት ናቸዉ።ሐማስ ድሮም-ዘንድሮም የእሥራኤል ጠላት ነዉ።

አልሲሲና እስራኤል ምን-ምን ምን ናቸዉ? በ1979 ሳዳት፤ ቤገን፤ ካርተር ነበሩ።በ1994 ቢል ክሊንተን-ካርተር ያደረጉትን፤ የዮርዳኖስ ንጉስ ሁሴን ቀዳማዊ-ሳዳት፤የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን-ቤገን ያደረጉትን ደገሙት።በክሊንተን ሸምጋይነት ሁሴይናና ራቢን የሠላም ዉል ሲፈራረሙ እሥራኤል በ1967ቱ ጦርነት ከዮርዳኖስ የቀማችዉን የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን ግዛት «አጠቃላዩ የፍልስጤሞች ጉዳይ መልስ ሲያገኝ ይፈታል» ብለዉ አለፉት።
የጋዛ ሕዝብ ለግብፅ እንደመቅረቡ ሁሉ-የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሕዝብ ለዮርዳኖስ ቅርብ ነዉ።የእሥራኤል ጦር ጋዛን መደብደቡን ዮርዳኖስ አልተቃወመችም።ድብደባዉን በመቃወም አደባባይ የወጣዉ የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሕዝብን የእሥራኤል ጦር ሲገድል-ሲደበድበዉ የአማን ገዢዎች ትንፍሽ አላሉም።ምክንያት እስራኤል ከእስራኤልም ይልቅ ለአማን ገዢዎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ የምትሠጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ ትቆጣቸዋለች።የረመላሕን የከንቲባነት ያክል እንኳን ሥልጣን ሳይኖራቸዉ «የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝዳንት» የሚል ሥም የተሸከሙት ማሕሙድ አባስ አምጠዉ አምጠዉ እስራኤል ጋዛን መዉረር ማጥፋቷን መቃወማችዉ አልቀረም።
ፈራ-ተባ እያሉ ያሰሙት ተቃዉሞ የሕዝባቸዉን ቁጣ፤ የእሥራኤሎችን ዱላ ለማብረድም ሆነ የአሜሪካኖችንም ይሁንታ ለማግኘት የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ድቀቱ።በስድስት ቀን ጦርነት ድፍን አረብን የረመረመችዉ እሥራኤልን በየሥስርቻዉ የሚሽሎኮሎኩት፤ የዉጊያ ዕዉቀት፤ ሥልጠና፤ በቂ መሳሪያ የሌላቸዉ የሐማስ ደፈጣ ተዋጊዎች ለሠወስት ሳምንት ያክል መዋጋታቸዉ ከፍልስጤሞች አልፎ በድፍን አረብ ተወዳጅ አድርጓቸዋል።

በ2006 ተድርጎ በነበረዉ ምርጫ አሸንፎ የነበረዉ ሐማስ ዳግም መግነኑ በአዉሮጳ ሕብረት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ አጥኚ ማቲያ ቶላዶ እንደሚሉት አቅመ ቢሱን መሪ ይበልጥ የሚሽመደምድ ነዉ።
«የሕዝብ ድጋፍን በተመለከተ እሳቸዉ (አባስ) በጣም እየተዳከሙ ነዉ።በዚሕ ሳምንት የተሰባሰበዉ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተዉ ከሥልሳ ከመቶ የሚበልጠዉ ሐማስን ሲደግፍ፤ ለአባስ ቡድን ድጋፉን የሰጠዉ ሃያ-ሁለት ከመቶ ብቻ ነዉ።»
አባስ በራሳቸዉ ሕዝብ ጨርሶ ከመንኮታኮት የሚድኑት አንድም ሐማስ ከጠፋ፤ ሁለትም የእሥራኤሎች ልብ ራርቶላቸዉ ማብቂያ የሌለዉን የሠላም ድርድር ከጀመሩ፤ ሠወስትም ከሐማስ ጋር የጀመሩትን ተጣማሪ መንግሥት ካጠናከሩ ብቻ ነዉ።የእሥራኤል ዱላ ሐማስን ማዳካሙ አይቀርም ጨርሶ ሊያጠፋዉ ግን በፍፁም አይችልም።
የኔትንያሁ መንግሥት ቢሆንለት ሁለት ደካማ የፍልስጤም ቡድናት (ሐማስና ፋታሕ) «ሲቦጫጨሩ» ዳር ቆሞ ማየትን እንጂ ፤ብዙዎች እንድሚሉት፤ አባስን ለማዳን ሲል ወደ ድርድር ይገባል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነዉ። ከሐማስ ጋር የጀመሩትን ጥምር መንግሥት ማጠናከር ለአባስ የተሻለዉ ምርጫ ነዉ።ግን ቶላዶ እንደሚሉት እስራኤል አትፍፈቅድም ።
«በእሥራኤል በኩል የአመለካከት ለዉጥ ይደረጋል ብዬ አላስብም።የእግረኛዉ ጦር ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ ከእሥራኤል ጥቃት ዋነኛ አላማዎች አንዱ ተጣማሪዉን መንግሥት ማፍረስ ነዉ።ሥለዚሕ እሥራኤል በቅርብ ጊዜ ዉስጥ በሐማስ የሚደገፍ መንግሥት ትቀበላላች ብዬ አላስብም።ይልቅዬ ዩናይትድ ስቴትስና አዉሮጶች ተጣማሪ መንግሥት መኖሩን ይበልጥ እያመኑበት መምጣታቸዉን አምናለሁ።»

በሁለት ሺሕ ስድስቱ ምርጫ ያሸነፈዉን ሐማስን ከሥልጣን ያስወገደዉ የእሥራኤል ጠመንጃ፤ የአዉሮጳና የአሜሪካኖች ማዕቀብ እና የነአባስ ሻጥር ነበር።
አረብ የሐይማኖት መሪ፤ የሐብት ልዕለ ሐያል ሐገር ካለዉ ሳዑዲ አረቢያን የሚቀድም የለም።የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ መንግሥት በጋዛ ሕዝብ ላይ የሚወስደዉን እርምጃ የፋርስ፤ የቱርክ፤ የፓሪስ፤ የለንደን፤ የበርሊን ሕዝብ ባደባባይ ሲያወግዝ ከሪያድ የተሠማ ነገር የለም።
ማዉገዝ መቃወሙ ቀርቶ የቀጠር፤የቱርክ፤ የአዉሮጳና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ለሠላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ሲዳክሩ የሪያድ ነገሥታት ጥምጣማቸዉ የተሸራተተባቸዉን ያክል እንኳን አልተንቀሳቀሱም።ምክንያት የግብፁን አምባገነን ገዢ ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ለማስወገድ አብይ ሚና የተጫወቱዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበርን ሪያዶች እኛም ጋ ይደገማል በሚል ሥጋት እንደጠላት ነዉ የሚያዩት።
ጄኔራል አል ሲሲ መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን ሲያስወግዱ ቀድመዉ የተደሰቱት፤ ለጄኔራሉ ዶላር ያንቆረቆሩት ሪያዶች ናቸዉ።ሐማስ የሙስሊም ወንድማማቾች ተቀጥላ ወይም ወዳጅ ነዉ።ሳዑዲ አርቢያ የሙስሊም ወድማማቾች ጠላት ናት።ሐማስ የእስራኤል ጠላት ነዉ።በየጠላትሕ ጠላት ስሌት የእስራኤልና የሳዑዲ አርቢያን ግኙነት- እርስዎ እንዴት ይፈርጁታል?
ሊቢያ፤ኢራቅ፤ሶሪያ እርስ በርስ እተጠፋፉ ነዉ።ቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ካዳፋት ወዲሕ በሁለት እግሯ ለመቆም ገና እየተዉተረተረች ነዉ።ነግሥታት የሚገዟት ሞሮኮ ከሪያድ፤ከአማንና ኩዌት የተለየች አይደለችም።የመን እንደ ሐገር ብትኖርም የምትተክረዉ የለም።አልጄሪያ እድሜም ጤናም የራቃቸዉን ሽማግሌ መሪዋን እያስታታመች

አረብ እርስ በርሱ እየተጠላለፈ-ይጥመለመላል።ሐያሉ ዓለም አንድም ተደፋፍጧል አለያም እስራእል እራሷን የመከላከል መብቷን «እስኪያቅለሸልሸን» እየነገረን ነዉ።በመሐሉ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተኩስ አቁሙ ይላል።ማንሰምቶት? በኮሶቮና በአፍቃኒስታን የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቶም ኮኒግስ እንደሚሉት አባላቱ ለየጥቅማቸዉ የሚሻኮቱበት ደካማ ማሕበር ሰሚ አይኖረዉም።
«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል።ድርጅቱ አሁን በጣም ደካማ ነዉ ማለት ይቻላል።አዎ ድርጅቱ ልክ እንደሚያስተናብራቸዉ አባላቱ ደካማ ነዉ።አባላቱ ደግሞ አሜሪካኖች፤ ወይም እስራኤሎች ብቻ አይደሉም።ጀርመን፤ ዮርዳኖስ እና ሌሎቹም በድርጅቱ ዉስጥ ያሉት ሁሉም ናቸዉ።»
ለጋዛ ሕዝብ የተከረዉ የለም።ካለም ተፋላሚዎች አንድም ዳግም እስኪደራጁ፤ ሁለትም አቅም እስኪፈታተሹ፤ ወይም ደክሟቸዉ በገዛ ፍቃዳቸዉ ተኩስ ማቆማቸዉ ነዉ። እስከ ዛሬ ጋዛ ሕፃናት፤ ሴቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አካለ ጎዶሎዎች ሳይለዩ ከአንድ ሺሕ ሰላሳ በላይ ነዋሪዎች አልቀዉባትል።ሰወስት ሺሕ ያሕል ቆስለዉባታል።እሥራኤል አርባ ሰዎስት ወታደሮች፤ ሁለት ሠላማዊ ስዎች አንድ የዉጪ እንግዳ ተገድለዉባታል።የዚያን ምድር ራብ፤ ጥም ለማስታገስ፤ የእስከዛሬዉ እስከሬን ደም ይበቃዉ ይሆን? (በነጋሽ መሐመድ ከሚሰናዳው ማህደረ-ዜና ጥንቅር የተወሰደ)

የ53 አመቱ አባት የጥቁር ሽብር ሰለባ አስገራሚ ክስተት

 

ቢቢኤን ራድዮ እንዳቀረበው፦

Muslim abatመንግስት ሀምሌ 11 በወሰደው የጭካኔ ተግባር ወጣቱ ወንዱ ሴቱ ህጻናቱ አዛውንቱ የጥቁር ሽብሩ ሰለባ ሁነዋል፡፡ የዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል የ53 አዛውንት ሰው ይገኙበታል፡፡ ይህ በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የርሳቸውን በከፍተኛ ድብደባ የቆሰለ ሰውነት ነው፡፡
 የ53 አመቱ ሰው ከቢቢኤን ሬድዪ ጋር የደረሰባቸውን ነገር አስመልክቶ ቆይታ አድረግዋል፡፡ ሙሉዉን ቆይታ ከራሳቸው አንደበት የምትሰሙት ይሆንና በመጠኑ ቀንጭበን በጽሁፍ እናካፍላችሁ፡፡

የጁምአን ሶላት በአንዋር መስጅድ ለመስገድ ዘግየት ብለው ስለደረሱ ውጭ አስባልት ላይ ነበር መስገጃ ካኪ ያነጠፉት፡፡ ምንም ተቃውሞ ባልተጀመረበት ሶላትም ባልተሰገደበት ሁኔታ ፖሊሶች መስግጃውን አንሱ በማለት ትንኮሳ ጀመሩ ይላሉ ግለሰቡ፡፡ እርሳቸውም ከእድሚያቸው አንጻር ሁኔታዎቹን ለማረጋገት ይሞከራሉ፡፡ በዚህ ሰአት ግን የፖሊሶቹ ምላሽ ያልጠበቁት ነበር ፡፡ በያዙት ዱላ ለሶላት የተሰበሰበውን ምእምናን መደበደብ ጀመሩ፡፡ እኚህ አባትን በርካታ ፖሊሶች ከበው ይደብድቡዋቸው ጀመር፡፡

የዱላ ውርጅብኝ የበዛባቸው አባትም ወደ መዲና ህንጻ ሩጠው ይገባሉ፡፡ ፖሊሶች ተከትለው ከገቡ በሁላ እየጎተቱ መሬት ላይ በመዘርጋት ዘግናኝ ድብደባ እንደፈጸሙባቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ከእድሜያቸው አንጻር በዚሁ እንኩዋን አልተዋቸውም፡፡ በጾመኛ አንጀታችው እየደበደቡ ወደ ልኩዋንዳ ፈጥኖ ፖሊስ ማሰልጠኛ ወሰዱዋቸው፡፡

ልኩዋንዳ ሲደርሱ እሳት እየነደደ ነበር ይላሉ፡፡ ከዛም የሴቶችን ጅልባብ ሀይማኖታዊ አልባሳት የሳቸውም ኮፍያ ጭምር በሳት ተቃጠለ፡፡ ወደ ሰፊ ሜዳ ከወሰዱዋቸው በሙሉ በግራና በቀኝ ዙርያውን ፖሊሶች ተደርድረው በመሃል እየቀጠቀጡ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመባቸው፡፡ በ120 በ90 ሜትር የሚሆነውን ሜዳ እያዞሩ ቀጠቀጡን ሲሉ ይናገራሉ አዛውንቱከድብደባውም ሌላ ኮፍያቸው ጫማቸው ተቃጥልዋል፡፡ አጸያፊ ስድብም ተሰድበዋል፡፡ ዱላቸው ተሰባብሮ ሲያልቅ እሳት ረመጡን እንዲረግጡ አድረገዋቸው፡፡ እስከ ሌሊቱ 9 ሰአት ይህ ሁሉ ሲፈጸምባቸው ጾመኛ ነበሩ፡፡
ዘጠኝ ሰአት ላይ አውጥተው ጣልዋቸው፡፡ ሌሊት ለተሃጁድ ሶላት የሚሄዱ ሰዎች ሲያገኙዋቸው አለቀሱ፡፡ የ53 አመቱ አባት ጀርባቸው በምስሉ እንደሚታየው ቆስሉዋል:: ራሳቸው ተፈርክስዋል፡፡

በመጨረሻም ምን ይላሉ ሲል የቢቢኤን ጋዜጠኛ አብዱረሂም ላቀረበላቸው ጥያቄ አዛውንቱ አስገራሚ ምላሽ ሰጡ፡፡ እንዲህም አሉ ”የደረሰብኝ ነገር የሰው ልጅ በወገኑ ላይ የሚፈጸመው ተግባር አይደለም፡፡ ይህም ሁኖ ግን ሰላማዊነታችንን በፍጹም መተ ው የለብንም፡፡ ድምጻችን ይሰማ ጁምአ ቢጠራ ሰባራ እጄን ወንድሞቼ ጋር እሰለፋሉ የምንፈልጋት ሰላማዊ ትግል ውጤት እስክትመጣ ሌላ ምን አደረጋለሁ፡፡ ለሙስሊሙ የማስተላልፈው ሰላማዊ ትግላችን መቀጠል አለበት፡፡ ይህን ስል ሁሉም ይደብደብ ማለቴ ሳይሆን እውነተኛ ነጻነታችን የምትከበርባት ሀገር እስክትመጣ መታገል አለብን፡፡ አንድነታችን ይዘን ጥያቄያችን እስኪመለስ እነሱ ይግደሉን እነሱ ይጨፍጭፉን እኛ በሰላማዊ ትግል አሻራችንን እናሳረፍ፡፡ በኔ የደረሰው ኢምንት ነው በጥይትም የተመቱ አሉ እንበርታ ይላሉ የ53 አመቱ አባት፡:

ለመስማት ተከታዩን ሊንክ ይጫኑ
http://goo.gl/pYP0hD
በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ሊንክ
http://goo.gl/NBc1Kx

posted by Gheremew Araghaw

ዶክተር ኢንጂነር› ሳሙኤል ዘሚካኤል ከሃገር ውጭ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ

ዶክተር ኢንጂነር› ሳሙኤል ዘሚካኤል ከሃገር ውጭ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ
– ዛሬ ማታ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠበቃል
የማይገባቸውን የትምህርት ደረጃና ማዕረግ ለራሳቸው ሰጥተው ያለአግባብ ጥቅም ሲያገኙ ቆይተዋል በሚል ሲብጠለጠሉ የቆዩት ‹ዶክተር ኢንጂነር› ሳሙኤል ዘሚካኤል በሚገኙበት ኬንያ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደዋሉና ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡
ግለሰቡ አደረጉት የተባለው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃንና በማኅበራዊ ድረገፆች ከተነሳ በኋላ በተለያየ መንገድ ገንዘብ ተጭበርብረናል ያሉ ሰዎች ክሳቸውን አቅርበው ለፖሊስ ቃል ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል መረጃዎቹ መነገር ከጀመሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ኬንያ ተጉዘው የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ የኢንተርፖል ቡድን እና ከኬንያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ከቀናት በፊት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል፡፡
የኢትዮጲካሊንክ ምንጮች እንደገለፁት ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ወደ ሃገር ቤት የሚመጡበት ሂደት ሲከናወን ቆይቶ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የተጠርጣሪውን ጉዳይ ለማስፈፀምና ወደ አዲስ አበባ ይዞ ለመምጣትም አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራር አባል ወደ ናይሮቢ እንደሄዱ ተነግሯል፡፡

posted by Belay Adugna

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት በአንዳርጋቸው ላይ ላወጣው ቪዲዮ ምላሽ ሰጡ

የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት ከ3 ቀን በፊት በቲቪ በማሳየት ላቀረበው ቪድዮ ምላሽ ሰጡ። ቪድዮው የተዘጋጀው የሰውን አንገት ለማስደፋትና ለፕሮፓጋንዳ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ብርሃኑ በአቶ አንዳርጋቸው እጅ ምንም ዓይነት ምስጢሮች እንደሌሎ ተናግረዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሰጥተውታል ለተባለው ፓስወርድም “የኦፕሬሽናል ጉዳዮችን የያዘ ፓስወርድ አይደለም፤” ያሉት ዶ/ር አንዳርጋቸው የሰጠው ፓስወርድ የተለያዩ ጥናቶችን የያዘ እንጂ ወያኔ ቢያገኘውም ባያገኘውም ምንም የሚጎዳ ነገር አይደለም ብለዋል። ዶ/ሩ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በኢሳት ቲቪ የተነጋገሩበት ቪድዮ ይኸው።

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት በአንዳርጋቸው ላይ ላወጣው ቪዲዮ ምላሽ ሰጡ

 

የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት ከ3 ቀን በፊት በቲቪ በማሳየት ላቀረበው ቪድዮ ምላሽ ሰጡ። ቪድዮው የተዘጋጀው የሰውን አንገት ለማስደፋትና ለፕሮፓጋንዳ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ብርሃኑ በአቶ አንዳርጋቸው እጅ ምንም ዓይነት ምስጢሮች እንደሌሎ ተናግረዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሰጥተውታል ለተባለው ፓስወርድም “የኦፕሬሽናል ጉዳዮችን የያዘ ፓስወርድ አይደለም፤” ያሉት ዶ/ር አንዳርጋቸው የሰጠው ፓስወርድ የተለያዩ ጥናቶችን የያዘ እንጂ ወያኔ ቢያገኘውም ባያገኘውም ምንም የሚጎዳ ነገር አይደለም ብለዋል። ዶ/ሩ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በኢሳት ቲቪ የተነጋገሩበት ቪድዮ ይኸው።