የመለስ “ትሩፋቶች” – መጽሃፍ ቅኝት (በክንፉ አሰፋ

August 7, 2014

ደራሲ፣ ኤርምያስ ለገሰ
ብዛት፣ 406 ገጾች
አሳታሚ፣ ነጻነት አሳታሚ ድርጅት

እንደ መንደርደርያ

በስፋት ሲወራለት የነበረውን ይህን መጽሃፍ ሙኒክ-ጀርመን ላይ ገዝቼ ለማንበብ እያፈላለግኩ ሳለሁ፤ አንድ ወዳጄ ይዞት አየሁ። የደበዘዘ የመለስ ፎቶ ያለበትን ይህንን መጽሃፍ የኦስሎው አበበ እጅ ላይ ነበር። ገና ሰላምታ ሳንለዋወጥ ነበር መጽሃፉን ከእጁ ላይ የነጠቅኩት። ታማኝ በየነም እዚያው አብሮን ስለነበር አስተያየቱን ጣል አደረገ። “መነበብ ያለበት መጽሃፍ” እንደሆነ አበክሮ ነገረኝ። ታማኝ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መጻህፍት በሙሉ እንደማያመልጡት አውቃለሁ። በዚህ አዲስ መጽሃፍ ላይ አንዳች አዲስ ነገር እንደሚኖር ከንግግሩ ለመረዳት አያዳግትም።

የመጽሃፉ መታተም ወሬ እንደተሰማ በደራሲው በአቶ ኤርምያስ ለገሰ ላይ የድጋፍና የተቀውሞ ድምጾች ከሁለት ጫፎች ይሰሙ እንደነበር አስተውያለሁ። ሁለቱም ጫፎች ለክርክራቸው የየራሳቸው መከራከርያ ነጥቦች ቢኖራቸውም መደምደሚያቸው አንዱ-ካንዱ ሚዛን የሚደፉ ሆነው አላገኘኋቸሁም። ማየት የሚገባን የጫነውን ሳይሆን ጭነቱን ነው እንዲሉ፣ መልዕክተኛውን ሳይሆን ይልቁንም መልዕክቱን አንብቦ የራስ ፍርድ መስጠቱ የሚመረጥ ይሆናል። ማንበብ ከጉዳቱ ጥቅሙ ነው የሚያመዝን። መረጃ ሁሉ አይናቅም። የብዙዎቻችን ችግር ከታማኞቻቸን የምናገኘውን መረጃ ብቻ ይዘን በዚያ ቁንጽል መረጃ ተንተርሰን ውሳኔ ለመስጠት መሞከራችን ይመስለኛል። ያ ስውዬ እንዳለው ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል። የኮ/ል መንግስቱን፣ የሻምበል ፍቅረስላሴን እንዲሁም የበረከት ስማዖንን መጽሃፍትስ ገዝተን አንብበን የለ? እንደዚህ አይነቶቹ መጻህፍቶች ሙሉ ሰው እንኳ ባያደርጉን ሚዛናዊ እንድንሆን ይረዱናል።

***
መጽሃፉ ሲገለጥ

በንዑስ ርዕስ “ባለቤት አልባ ከተማ” ተብሎ የተሰየመውን “የመለስ ‘ትሮፋቶች’” እነሆ አነበብኩት..

ደራሲው፣ ኤርምያስ ለገሰ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሂሳብ ትምህርት የባችለር ዲግሪውን እንደያዘ መከላከያ ሚ/ር ውስጥ ተቀጥሮ ዝዋይ በሚገኘው የመከላከያ ኮሌጅ ከፍተኛ መኮንኖችን ለማሰልጠን ተጓዘ። በካምፑ ያሉ አብዛኞቹ መኮንኖች ከአምስትኛ ክፍል ያልዘለሉ እንደሆኑም በገጽ 209 ያስነብበናል። ወጣቱ ካድሬ እነዚያን መሃይም መኮንኖች የተፈጥሮ ሳይንስ ሊያስተምራቸው እንዳልሄደ ግልጽ ነው። ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ… እንዲሉ ከበረሃ የመጡ ነባር ታጋዮችን የድል አጥቢያው ካድሬ የራሳቸውን ርዕዮተ-አለም ሊለቅባቸው መሄዱ ደግሞ የበለጠ ግርታ ይፈጥራል።

ደራሲው የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ወንጌል የተቀበለው የአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነበር። እዚያ በተማሪ ስም ተመድቦ የሚሰራ ሰላይ ካድሬ ይህንን የቅጥፈት ፍልስፍና ሰብኮ እንዳጠመቀው በገጽ 192 ላይ አስፍሯል። በአራት ኪሎ ቆይታው ከሂሳብ ትምህርቱ ጎን ለጎን ቀዩዋን መጽሃፍ ሲበላት ከርሞ ኖሮ፤ የህወሃት ሃዋርያ ሆኖ እነሆ ወንጌሉን ሊሰብክ ተሰማርቷል።

ይህንን ለማድረግ ታድያ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በስሱ ሳይሆን እስከ አንገቱ ድረስ መጋት ይኖርበታል። የድርጅቱ አይነተኛ ርእዮተ-አለም የሆነውን የባንቱስታን የክልል አገዛዝ እና የዘር ፖለቲካን አቡክቶ ማብሰል ይጠበቅበታል። ከፍ ሲል ደግሞ ኢህአዴግኛ ቋንቋ መናገር የግድ ይሆንበታል – መስፈርቱን ለሟሟላት። በገጽ 327 ላይ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ቀጥ አድርጎ ሰላቆመው ምሰሶ ሲገልጽ፤ “በራስ ያላመኑበትን ነገር መናገር – ለህሊና የሚከብድ” ብሎታል። አለፍ በሎም እንደ ሂትለሩ ጎብልስ ውሸትን እየደጋገሙ ህዝብን ለማሳመን መሞከር (ገጽ 389) እንደሆነ ይነግረናል።
ወትሮውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ወደ ኢህአዴግ ጎራ የሚገባ ተማሪ በማህበራዊ ኑሮው ላይ ምን ያህል አደጋ እንደሚጋረጥበት በውስጡ ያለፍነው የምናውቀው ጉዳይ ነው። አንድ ተማሪ ኢህአዴግ አባል ከሆነ መጀመርያ ከህብረተሰቡ ጋር ይራራቃል። ከዚያ ከመርህ ጋር ይጋጫል። በመጨረሻም ከራሱ ጋር ይጣላል።

ኤርምያስ ያውም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሆኖ ለኢህአዴግ በካድሬነት የመጠመቁ ስሜት ከምን ሊመጣ እንደቻለ ለማወቅ ያጓጓል። በመጽሃፉ ውስጥ ይህቺን ጉዳይ እንደዋዛ ሳይጠቅሳት አልፏል። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ አንድ እና አንድ ሶስት ነው የሚሆነው። እንደሁኔታው አራትም አምስትም ሊሆን ይችላል።

ወጣቱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካድሬ መሆን ደግሞ በሂሳብ ትምህርት አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው የሚለውን ስሌት ለድርድር ማቅረብ ግድ ይለዋል። እዚያ መርህ እና እውነት የሚባል ነገር አይሰራም። ይህንን ደግሞ ኤርምያስ ራሱ በመጽሃፉ ውስጥ ባነሳቸው ርዕሶች ሁሉ ያረጋግጥልናል። “ከኢህአዴግ ጋር ያቆራረጠኝ ከራሴም ጋር ቅራኔ ውስጥ የዘፈቀኝ ሕግ ይህ ነበር።” (ገጽ 1) ሲል “እውነት የተደጋገመ ኩሸት ነው” የሚለውን የድርጅቱን የመጀመርያ ህግ ያነሳል። ህጉን በትክክል ገልጾታል።

ልዩነቱ ኤርምያስ የባነነው ከ12 አዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። በነዚያ አመታት ከተራ ካድሬነት አልፎ ልዩ-ልዩ ሃላፊነትን ተሸክሞ በሰባራው ሃዲድ ረጅም ተጉዟል። ከአዲስ አበባ የምክር ቤት አባልነት እስከ መንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ የሚደርስ የስልጣን ተሸክሟል። በመጽሃፉ የዘረዘራቸው ዘግናኝ ዝርፊያዎች ሲካሄዱ አይንና ጆሮውን ከልሎት የነበረው ይህ ሸክም ይሆን? በገጽ 303 ላይ “እኔ ኢሕአዴግ ነበርኩ። ያውም እውነቱ እስኪገለጥልኝ በእምነት የምተጋ ካድሬ። ….10ሺ የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እያጠመቅኩ ኢሕአዴግ አርገያለሁ።” ብሎናላ!

***

መጽሃፉ በስምንት ክፍሎች ተመድቦ በሃያ አምስት ምዕራፎች ተሸንሽኗል። በዋናነት ግን በሶስት ጉዳዮች ላይ እያጠነጠነ በዚህ ዙርያ ተዛማች የሆኑ መረጃዎችን ያስነብበናል። በአንዲት ጀምበር ቢሊየነር የሚያደርገው የባለቤት አልባዋ አዲስ አበባ የመሬት ዘረፋና የምርጫ 92/97/2000 እንድምታዎችን በግንባር ቀደምትነት ይተነትናል። እንዲሁም የባድመ ጦርነት አስከትሎ ያመጣቸውን መዘዞችን በስሱ ለመዳሰስ ሞክሯል።
የጨለማውን አሊ አብዶ ዘመን በግርድፉ ይዳስሳል። የካዛንችሱ ስውር መንግስት አሊ አብዶን በርቀት እንዴት ይነዳው እንደነበር ያወሳል። የበለጠ ትኩረቱ ግን በአርከበ እቁባይ አስተዳድር ችግሮች ላይ ነው። በነዚህ ዘመናት ዘረፋው ግዙፍ፣ ችግሮቹም ውስብስብ ነበሩ። በእውነት ለመናገር በመጽሃፉ የተነሱት በደሎች እና ዘረፋዎች የአደባባይ ምስጢሮች ናቸው። አብዛኞቹ ከግሉ መገናኛ ብዙሃን የተደበቁ አልነበሩም። ይህ መጽሃፍ ዝርፍያዎቹ መቼ፣ እንዴት እና በማን ተፈጸሙ ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ የቀድሞዎቹን መረጃዎች የተሟላ ያደርጋቸዋል። ጉዳዮቹን በስፋት እና በጥልቀት ለማወቅ የሚያስችል ግንዛቤም ይሰጠናል። ከንቲባ አሊ አብዶ ዘመን ሁላቱን ታላላቅ እምነቶች ለማጋጨት እሳቤ ሆኖ፣ በታቦት ማረፍያዎች ሳይቀር መስጊድ እንዲሰሩበት ይደረግ እንደነበር ቀደም ብሎ ተዘግቧል። አርከበ እቁባይ ከንቲባ ሆኖ ሲሾም የካቢኔ አባለቱን ከትግራይ ጭኖ ባመጠቸው መሃይማን ካድሬዎች መሙላቱም አዲስ መረጃ አይደለም። የጠገበው ጅብ ሲሄድ የራበው መተካቱን የማያውቅ የለም። የኤርምያስ መጽሃፍ ግን መረጃውን በማስረጃ እየደገፈ ይተርክልናል። ለተራው አንባቢ ትርጉም ባይሰጥም፤ የበርካታ ሹማምንት ስሞችን በመጽሃፉ ተደርድረው እናገኛለን።
የመለስ “ትሮፋቶች” ደረቅ የፖለቲካ ትንተና ላይ የሚያተኩር ያለመሆኑ መጽሃፉን ያለትንፋሽ እንዲነበብ ያደርገዋል። በአንድ ጎኑ ጥርስ የማያስከድኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንጀት የሚያቃጥሉ እውነታዎችን ይዟል።

ተወርቶ የማያልቀው የአርከበ እቁባይ ታሪክ ውስጥ የካድሬ ተስፋ ብርሃን ጉዳይ ሰፍሯል። ተስፋ ብርሃን መስማት የተሳነው ህመምተኛ ነው። አርከበ ከመቀሌ አስጭኖ ያስመጣው ካድሬ። ሲቪል ሰርቪሱን፤ ትምህርት ቢሮን እና አጠቃላይ አቅም ግንባታውን እንዲመራ ሃላፊነት ተሰጥቶታል። ገብረተንሳይ የሚባለው ሌላኛው ካድሬ በአንድ ግምገማ ላይ “አንተ ደንቆሮ ነህ። ካንተ ጋር እንዴት እንደምሰራ አይገባኝም?” ይለዋል። መስማት የተሳነው ተስፋብርሃን መልሶ “ገብረተንሳይ ልክ ነው የመምህራን ስልጠና መስጠት አለብን።” አለው (የመለስ “ትሮፋቶች” ገጽ 132)። ደራሲው በየግምገማዎቹ ይከሰቱ የነበሩ እንደነዚህ አይነት ጥርስ የማያስከድኑ ትውስታዎችን በመጽሃፉ ውስጥ አስፍሯቸዋል። በተላይ የካድሬ ጨነቀ ታሪክ (ገጽ 150-155) ‘ጧ ‘ አድርጎ ከማሳቁ ባሻገር ስርዓቱ በሕዝብ ላይ ምን ያህል እየቀለደ እንደሆነ ያሳየናል።

በገጽ 224-225 የሰፈረው የአቦይ ስብሃት ጉዳይም ጥርስ በጣም ያስቃል።

ጸሃፊው በአብዛኛው ርእሶቹ እንደመነሻ የሚያደርገው የበረከት ስምዖንን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” እንደሰበዝ የሚመዘዙ ስንኞች በመጠቃቀስ ነው። በአንባቢያን ዘንድ ብዝም ትኩረት ያልሳበው የበረከትን መጽሃፍ በውሽት የታጨቁ ድርሰቶች አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። በከፊል በማስረጃ እያስደገፈ ነው ድርሰቱን ያጣጣለው። የበረከትን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ያላነበበ ካለ ዋና ዋናዎቹን የበረከት መርዘኛ መልዕክቶች ከነማፍረሻቸው በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ያገኛቸዋል። ኤርምያስ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በበረሃ ከተጠመቁት የህወሃት ካድሬዎች ጋር እኩል ቀርቦ ከማእዱ ሊቋደስ ከቶውን እንደማይችል እርግጥ ነው። በዚያ ላይ ከቅዱሰ-ቅዱሳኑ ለመግባት የዘር መስፈርቱን አያሟላም። እንደማንኛውም የድል አጥብያ ካድሬ በታማኝነቱ መጠን እነ በረከት እውቀቱን ተጠቅመውባታል። በሃገሪቷ ወሳኝ ጉዳዮችና ውሳኔዎች ላይ የመጀመርያ መረጃ ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው። ከመጽሃፉ እንዳየነው አብዛኞቹን መከራከርያ ነጥቦቹ የሚያተኩሩት ከየግምገማዎቹ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ነው። በምኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ላይ ያለ ሰው ማወቅ የሚገባውን እንኳን አያውቅም። ለምሳሌ በገጽ 376 ላይ በኢትዮ-ኤርትራና ኢትዮ-ሶማልያ ጦርነት ክ120ሺህ የሃገራችን ወጣቶች ማለቃቸውን በይፋ የሰማው በአንድ ግምገማ ላይ ከወ/ሮ አዜብ መሆኑን ይናገራል።

በመጽሃፉ አልፎ አልፎ በቅንፍ የቀረቡ መረጃዎች ውስጥ፤ የሃይሌ ገ/ስላሴ አድርባይነት፣ የቴዲ አፍሮ በአዜብ ጥርስ ውስጥ መግባት እና ጉዳዩን ይዞ የነበረው ካድሬ ዳኛ ልዑል፣ የፕ/ር መረራና ዶ/ር በየነ ጉዳይ የሚያስደምሙ ናቸው። “ጉራጌ መራሽ አብዮት” ያሉትን ነቅናቄ ለመቀልበስ በተከወነው ሴራ (ገጽ 232-234) ታታሪውን የጉራጌ ህዝብ ዛሬ ከጫወታ ውጭ እንዳደረገው ይገልጻል።

የአያት መኖርያ ቤት ድርጅትን (ሪል ስቴት) ሙስና ለመታደግ፤ እነ በረከት ስምዖን የግሉን ፕሬስ ሳይቀር በማሳተፍ የሰሩት ድራማ (ገጽ 326) ለአንባቢው አዲስ ነገር ነው። የዚህ መጽሃፍ ደራሲ፣ ኤርምያስ ለገሰ በዚህ “አሳዛኝ” በሚለው ጥፋት ላይ መሳተፉን በጸጸት ጽፎታል። ያንን ሁሉ አመት ከህወሃት ጋር በእምነትና በትጋት ሲሰራ እንደነበር ቢነግረንም ከዚህ ውጭ የተናዘዘው ሃጥያት ግን የለም።

በምኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ላይ ካለ ሰው የምንጠብቀው ከዚህ ላቅ ያለ ምስጢር ነበር። መጽሃፉ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ብዙ ትኩረት አልሰጠም። ሌላው ቢቀር የግል ፕሬሱ ይዘግባቸው የነበረው በካዛንችዙ ስውር መንግስት ስር የሚሰሙ ሰቆቃዎች፣ ስቃይና ግድያዎች ጸሃፊው እንደዋዛ አልፏቸዋል። እንደ እንጉዳይ ተክል በአንድ ሌሊት ብቅ ያለው የአባይ ጉዳይ ላይ ኤርምያስ አንድ ነገር ይላል የሚል ግምትም ነበረን። ይህንንም በዝምታ አልፎታል። ምናልባት የምስጢሩ ተቋዳሽ አይሆን ይሆናል። ምናልባትም በቀጣዩ ማስታወሻው ይመለስበት ይሆን ይሆናል። ስለ ሃይሌ ገብረስላሴ አድርባይነት በሚገልጸው ክፍል (ገጽ 285) ስለ አትሌቱ፤ “እንቁ እግር፣ አድርባይ ጭንቅላት” የሚል ርእስ በሚቀጥለው ማስታወሻ እመለስበታለሁ ብሎናል። ይህም ደራሲው ቀጣይ ስራ እንዳለው ያመላክተናል።

መጽሃፉ በርካታ የፊደል ግድፈቶች ይታዩበታል። አንዳንዶቹ ግድፈቶች የመልዕክቱን ትርጉሙ ሁሉ ቀይረውታል። ከዚያም አልፎ፤ በአማርኛ ተስተካካይ ፍቺ ያላቸው እንደ ዲሞቢላይዜሽን፣ ኔትወርክ፣ ኦረንቴሽን፣… የመሳሰሉ የባዕድ ቃላት በአማርኛ ተዛማጅ ትርጉም አልያም በቅንፍ ቢቀመጡ ይመረጥ ነበር።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: