ኢትዮ ቴሌኮም አውቆ እንዳለወቀ መሸፋፈን ይተው

 

በአገራችን የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ከትክክለኛ ሥራው ይልቅ ነጋሪት ጉሰማው በአያሌው የሚልቅበት ዘርፍ ቢኖር የቴሌኮም ዘርፍ ነው፡፡

ትንንሽ ድሎች ለትልልቅ ችግሮች መፍትሔ ይሆኑ ይመስል እነሱን ሲያቆላምጡ መኖርም የዘመኑ ተግባር ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች በሞባይል የገንዘብ ዝውውር ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ኑሮ ለውጥ ማምጣት ሲችሉ፣ የእኛ አገር ቴሌኮም ግን አበው እንደሚሉት ‘‘ከቀንድ ቆጠራ’’ ብዙ ሊዘል አልቻለም፡፡ ዛሬም የአገራችን ቴሌኮም አገልግሎት ከመሻሻል ይልቅ የሞባይል ተጠቃሚ ብዛት መቁጠር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የዘርፉ የትግበራ ሪፖርቶችም የአገልግሎት ጥራትን ችላ ባሉ ቁጥሮች የተሞሉ ናቸው፡፡ 

ምንም እንኳ ይህ ልምድ በመጀመሪያው የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በመካሄድ ላይ ባለው የሁለተኛ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ግን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን እያስተዋልን፣ ኢትዮ ቴሌኮምም ቢሆን በውስጡ ያሉበትን ችግሮች ለመሸፈን መላ ያገኘ በሚመስል ሁኔታ ትኩረቱ ይህንን አስፋፋሁ፣ ያንን ቀጠልኩ፣ ይህንን ጀመርኩ፣ በውጤቱም ይህንን ያህል ሞባይል ተጠቃሚ ኖረ የሚል ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በመሠረቱ መሬት ላይ ያለው ሀቅ የተስፋፋም፣ የተቀጠለም፣ የተጀመረም ቢኖር እንኳ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሞባይል ጥራት ሰዎችን ለማገናኘት የማይመጥን መሆኑ ነው፡፡ መቆራረጥ የበዛበት አማራሪ የኔትወርክ ሥርዓት ይዞ መመሰጋገን አበው ‘‘በየወንዙ መቀደስ የተኛን ሰይጣን ለመቀስቀስ” እንዲሉ፣ የሕዝብን ብሶት ለማባባስ መንስኤ ይሆናል፡፡

 መዲናችን አዲስ አበባ ተሠራላት እየተባለ ከሚዘመርላት የ‘‘3G’’ ኔትወርክ መጠቀም ቀርቶ ሕዝቡ ብሩን ከእጁ ላይ ከሚሞጨልፈው የተዛባ የስልክ ዋጋ አሰባሰብ ሥርዓት፣ እንዲሁም ዘገምተኛነቱ እየተባባሰ ከመጣው የስልክ ላይ ኢንተርኔትና ለአራዶች እንኳ ከማይገመተው የአከፋፈል ሥርዓት ውጪ ጠብ ያለ ነገር አላየንም፡፡ ኅብረተሰቡን ተስፋ ሲመግቡት የነበሩት አትዮ ቴሌኮምና ተቋራጩ የቻይና ኩባንያ ሁዋዌና ዜድቲኢ ያሉት ሰኔ ደርሶ ሪፖርት ሲያደርጉ፣ ከሌላ ተስፋ ውጪ ሊያበስሩን የቻሉት የሚጨበጥና የሚዳሰስ የኔትወርክ ጥራት አልታየም፡፡ ሁለቱም አካላት ያልተረዱት ወይም የዘነጉት የሚመስለው ግን ሕዝቡ በጥራት ችግር መማረሩ አሁንም የቀጠለ መሆኑን ነው፡፡

ከልማዳዊ የፕሮጀክት አፈጻጸም ጀርባ ያሉትን ችግሮች መመልከቱ ምናልባትም ፊት ለፊት ለምናያቸው የተጋነኑ የግንኙነት ሥራዎች ጀርባ ያሉትን ክፍተቶች ለማየት ያበጃል፡፡

በአዲስ አበባ ተተገበረ የተባለው የ‘‘3G’’ አገልግሎትም ሆነ ሊጀመር ነው እየተባለ የሚወራለት የ‘‘4G’’ አገልግሎት በቻይናው ሁዋዌ የሚሠሩ ናቸው (ዜድቲኢ በ‘‘3G’’ ይሳተፋል)፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ሥራውን ሲያከናውን የነበረው ይህ ኩባንያ ከአቅም ችግር ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙት ቢታዩም፣ አትዮ ቴሌኮም ግን ባልተለመደ ሁኔታ በዝምታ ሲያልፈው የተስተዋለባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው የሁዋዌ ሠራተኞች ጥብቅ የሆኑትን የቴሌኮም ጣቢያዎች በአንድ መታወቂያ እየተጠቀሙ ሲገቡባቸው ዝም በማለት ያለፈው ኢትዮ ቴሌኮም፣ የተከተለውን የተሳሳተ የስቴሽኖች ቅየራ ለማስተካከል የሞራል የበላይነት አልነበረውም፡፡ በተሳሳተ የስቴሽኖች ቅየራ ምክንያት የተበጠበጠውን የኔትወርክ ሥርዓት ለመሸፈንም  አትዮ ቴሌኮም የተጠቀመው የተለመደውን የሕዝብ ግንኙነት መሣርያውን ነው፡፡ ጥሬው ሀቅ ግን የስቴሽን ቅየራ ልምዱና በቂ የሰው ኃይል ያልነበረው ሁዋዌ ቅየራውን ዓለም ከሚመራበት የቅየራ ቴክኒክ ጋር በማይጣጣም መንገድ ማስኬዱና ይህም ጠቅላላውን የከተማውን ኔትወርክ መበጥበጡ ነው፡፡

በዚህ ሳያበቃ ይህ ጥራት የጐደለው የስቴሽኖች ቅየራ የክፍያ ሥርዓቱን በጠበጠውና ካርድ መሙላት፣ ቀሪ ሒሳብን ማወቅ፣ ካርድ መዋዋስ እንዲሁም መደወል ከተራ ተግባሮች ወደ ራስ ምታትነት ተቀየሩ፡፡ ከዚህ የባሰው ደግሞ ይህንን ችግር ለማስተካከል በሚል ኩባንያው የወሰደው ዕርምጃ ዜጎችን ላልተጠቀሙበት የቴሌኮም አግልግሎት ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዱ ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮም የትኩረት አቅጣጫ የደንበኛ መማረሩ በመጠኑም ቢሆን ረግቦ ማየት በመሆኑ ‘‘ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ብሎ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ለፕሮጀክት ፈጻሚው ችግር መሸፈኛነት መጠቀምን መርጧል፡፡ ችግሩ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ሌላው ምናልባትም ገዘፍ ያለው ችግር ደግሞ አዲሱን የ‘‘3G’’ እና ‘‘4G’’ መሠረተ ልማት ይደግፋሉ ተብለው የተተከሉትን ማማዎች ከመተከላቸው በፊት በቂና ጥራቱን የጠበቀ የአየር ፀባይ፣  የአፈር፣ የዝናብ፣ የነፋስ እንዲሁም የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጥናቶች መደረግ ቢኖርባቸውም፤ አሠራሩ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነበር፡፡ ተገቢ የሆኑትን የመሬት ሁኔታ ጥናቶች ሳያካሄድ የተሠሩትና በግብፅ ተቋራጭ (ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ) ለሲቪልና ለኮንስትራክሽን ሥራዎች በአንድ ወጥ የተመረቱት ማማዎች ከተተከሉ ከቀናት በኋላ እንደ ሸንበቆ እየዘመሙ መውደቃቸውና ለሕዝብም የአደጋ ሥጋት መሆናቸው ከኢትዮ ቴሌኮም ዕውቅና ውጭ አልነበረም፡፡ የማማዎቹ አመራረትም ሆነ ቀድሞ የተሠራው የመሬት ሁኔታ የጥራት ችግር እንደነበረባቸውም ኢትዮ ቴሌኮም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክት አመራሩ ትኩረት የደንበኛን መማረር መቀነስ በመሆኑ፣ ይህንን የመሰለ መሠረታዊና ከትንንሽ የቴሌኮም  ተቋራጮች እንኳ የማይጠበቅ የቴክኒክ ስህተት እያየ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን መርጧል፡፡

ከሁሉም የሚገርመው የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት አመራሮች ይህንን መሠረታዊ ችግር እንደ መደበኛ ችግር ይቆጥርላቸው ዘንድ ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ ይኼ መቼም ሕዝብን እንደ አላዋቂ ከመቁጠር ውጪ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ ቁጭ በሉና ላሞኛችሁ እንዳለው ሞኝ፡፡

የቴሌኮም ማማዎችን ወደ ሸንበቆነት የመቀየር ችግር በተነፃፃሪ ተደራሽ ሊባል በሚችለው አዲስ አበባ ውስጥ እንዲህ ከሆነ፣ አገራዊ ፕሮጀክቱ ሲተገበር እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ታዲያ የችግሩን ባለቤት መቅጣት ይሻላል ወይስ ችግሩን መሸፋፈን?

የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ልማዳዊ የእከክልኝ ልከክልህ ዓይነት መሆኑ ነው ዋናው ችግር፡፡ ታዲያ ምነው መንግሥትስ ዝም ማለቱ? አገሪቱ ለዘርፉ የምታወጣው ወጪ ምንም እንኳ በብድር የተገኘም ቢሆንም ከነወለዱ ይከፈል የለምን?   

(ክብረት ረዳ፣ ከአዲስ አበባ) 

ሪፖርተር 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s